Ethiopian News and Views.

በአጋጣሚዎች የታጀበው የሊቀ ማዕመራን አበባው ይግዛው የቀብር ሥነ – ሥርዓት ተፈፀመ

(ሚያዚያ 27/1933 – ጥቅምት 6/2005)

በአጋጣሚዎች የታጀበው የሊቀ ማዕመራን አበባው ይግዛው የቀብር ሥነ – ሥርዓት ተፈፀመ

ከአገኘሁ መኮንን

ባደረባቸው ህመም ምክንያት ለንደን በሚገኘው የሐመርስሚዝ ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ የቆዩት ሊቀ ማዕምራን አበባው ይግዛው በተወለዱ በ72 ዓመታቸው ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ሊቀ ማዕምራን አበባው ይግዛው ታላቅ የቤተክህነት ምሑር፣ ሲበዛ ሀገር ወዳድ፣ የሰላ ብዕር የነበራቸውና የቅኔ ባለሙያ ከመሆናቸውም በላይ አጅግ ደግ ሰው ስለነበሩ በለንደን ነዋሪ ዘንድ የታወቁና የተከበሩ ሰው ነበሩ። በዚህም ምክንያት ታምመው ሆስፒታል በነበሩበት ወቅት የመታመማቸው ወሬ በይፋ ባይነገርምና በኋላም ወሬው ቀስ በቀስ ከሾለከ በኋላ በሆስፒታሉ ላይ ጫና ላለመፍጠር ሲባል “መጠየቅ አይቻልም” እየተባለ የጠያቂውን ብዛት ለመገደብ ጥረት ቢደረግም እንኳን የጠያቂያቸው ብዛት የሆስፒታሉን ሠራተኞች እጅግ ያስደነቀ ነበር። በፅናታቸው፣ በጉብዝናቸውና በጥንካሬያቸው ሕዝቡን ያስደነቁት ባለቤታቸውና ልጆቻቸውም የመጨረሻዋ እስትንፋሳቸው እስካቆመችባት ሰዓት ድረስ አንድም ቀን ሰለቸን ሳይሉ ከአልጋቸው ዙሪያ ንቅንቅ ሳይሉ አስታመዋቸዋል።

ማቹ ሊቀ ማዕመራን አበባው ይግዛው ዓርብ ጥቅምት 9 ቀን 2005 ዓ.ም. በለንደን ደብረ – ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ብዙ ሕዝብ በተገኘበት ፀሎተ – ፍትሃት ተደርጎላቸዋል። ቀኑ የሥራ ቀን ከመሆኑም በላይ፣ አርብ ለሚደረገው ፀሎተ – ፍትሃት ጥሪ የተደረገው ሐሙስለት ቢሆንም ከፍተኛ ቊጥር ያለው ሕዝብ ተገኝቶ ፀሎተ – ፍትሃቱን ተከታትሏል።

የፀለተ – ፍትሃቱ እንዳበቃ የሊቀ ማዕማራን አበባው ይግዛው የሕይዎት ታሪክ በጓደኛቸው በአቶ ተክለ ማርያም መንግሥቱ ተነብቧል። አቶ ተክለማርያም በእንባ አየታጠቡ አንደምንም አንብበው እንደጨረሱ መሪጌታ ሐዲስ የተባሉ ካህን የሊቀ ማዕምራን አበባውን ሊቅነት የሚገለጽ ቅኔ በግዕዝና በአማርኛ አቅርበዋል። እንደ አቶ ተክለ – ማርያም ሁሉ መሪጌታ ሐዲስም ቅኒያቸውን ሲያቀርቡ ፊታቸው በእንባ እየታጠበ ነበር። በመቀጠልም ዲያቆን መንገሻ መልኬ ለሊቀ ማዕምራን መታሰቢያ የሚሆን ግጥም አቅርቧል። ሦስተኛው አቅራቢ የሊቀ ማዕምራን አበባው መምህራን ከነበሩት ውስጥ አንዱ የነበሩት ታዋቂው የቅኔ መምህር፣  የመምህር ጌጡ ተሰማ ልጅ አቶ ኆኅተብርሃን ጌጡ ነበር። የመጨረሻው ግጥም አቅራቢ ሊቀ ማዕምራን አበባው ይግዛውን ከልጆቻቸው ባልተለየ ሁኔታ ያስታመመው ጎረቤታቸው አቶ ግርማ ወ/ማርያም ነበር። ግርማ የውስጥ ስሜቱንና እውነተኛ ፍቅሩን የገለፀበትን ግጥም ያነበበው የለቅሶ ሳግ እየተናነቀውና ፊቱ በእንባ እየታጠበ ሲሆን፣ የእርሱ ማንባትና የግጥሙ ይዘት የሕዝቡን ስሜት ኮርኩሮ በጣም አስለቅሶታል።በዚሁ የፀሎተ – ፍትሃት ላይ የኢሳት አባላት የአበባ ጉንጉን አበርክተዋል።

ፀሎተ-ፍትሃቱ እንዲህ በደመቀ ሁኔታ እንደተጠናቀቀ ሁሉ በሂትሮው አውሮፕላን ማረፊያ የተደረገው የአሥከሬን አሸኛኘትም በጣም የተሳካና ብዙ ሕዝብ የተገኘበት ነበር።

እንዲህ በደመቀ መልኩ የተሸኘው የሊቀ ማዕምራን አስከሬን ጥቅምት 10 ቀን ቅዳሜ ጠዋት አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በዘመዶቻቸውና በወዳጆቻቸው አቀባበል ከተደረገለት በኋላ ከቀኑ 12 ሰዓት ሲሆን ወደ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ተወሰደ።

ሊቀ ማዕምራን አበባው ይግዛው የዋህ፣ ደግና እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆናቸው የቀብራቸው ሥነ-ሥርዓት በእግዚአብሔር ኃይል በብዙ አጋጣሚዎች የተከበበና እጅግ ያማረ እንዲሆን አድርጎታል። ለመሆኑ እነዚህ አጋጣሚዎች ምን ምን ናቸው?

  1. ምንም እንኳን ዕቅዱ በንድፈ-ሃሳብ ደረጃ በአቡነ ቴዎፍሎስ ጊዜ ይነደፍ እንጅ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰበካ ጉባኤን ያቋቋሙትና በተግባር ያዋሉት ሊቀ ማዕምራን አበባው ይግዛው የኢትዮጵያ ቤተክህነት ዋና ሥራ አሥኪያጅ በነበሩበት ጊዜ ነበር። ይህም እርሳቸው ያቋቋሙት የሰበካ ጉባኤ ዓመታዊ ጉባኤውን ለማድረግ ከየሀገረ-ስብከቱ መጥቶ አዲስ አበባ ይገኝ ነበር። በሕመም ምክንያት አንድ ጳጳስ ባቻ ሲቀሩ በስተቀር በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሁሉም ጳጳሳት በሚያስገርም ሁኔታ በሊቀ ማዕምራን አበባው ይግዛው ፀሎተ-ፍትሃትና ቀብር ላይ ተገኝተዋል።

  2. ግብጽ ይኖሩ የነበሩ ሌላ አንድ ጳጳስ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው የሁለቱም ፍትሃት አብሮ በአንድ ላይ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል። ከምሽቱ 3 ሰዓት ጀምሮ ማኅሌት ተቁሟል፤ ፀሎተ-ፍትሃት ተደርጓል፤ አደራረስም ተደርሷል።

  3. የዓለም አብያተ – ክርስቲያናት የሙታንን ቀን በፀሎት አስበውበት የሚውሉበት ቀን ደንግገዋል። ያቺም ቀን ጥቅምት 11 ቀን ነች፦ ሊቀማዕምራን አበባው ይግዛው የተቀበሩባት ቀን!

  4. ሌላው አስገራሚ ገጠመኝ ደግሞ የሊቀ ማዕምራን አበባው ይግዛው አስከሬን ያረፈበት ቦታ ነው። ቦታው ከቤተክርስቲያኑ ሕንፃ በስተ ምሥራቅ ሆኖ ወደ ቤተልሄም ሲገባ በስተግራ ያለ ቦታ ነው። የሊቀ ማዕምራን አበባው ባለቤት ወ/ሮ ሐረገወይን መንገሻ በመገረምና የእግዚአብሔርን ታላቅነት በማድነቅ ምሥክርነታቸውን ሲገልፁ፦ “ይህች ቦታ ዱሮ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪ እያለ የግል ጥናቱን ገዳም ብሎ ያጠናባት የነበረች ቦታ እንደነበረች ነግሮኛል” ብለዋል።

ታዋቂው ባለቅኔ መጋቤ ሚስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሄ እንባቸው እንደ ጎርፍ በጉንጫቸው እየወረደ “ባለቅኔው እርሱ፣ ገጣሚው እርሱ፣ የሥነ – ጽሑፉ ሰው እርሱ፣ በእርሱ ቦታ ስመዘን አኔ ማን ነኝና ነው ለእርሱ ቅኔ የምቀኘው?” እያሉ ሊቀ ማዕምራን የሰበካ ጉባኤን በማቋቋም ለካህናት የደመወዝን ሥርዓት የዘረጉና ቀን ያወጡላቸው ናቸው በሚል አንደምታ ቅኔያቸውን ሲያወርዱት ሕዝቡ በእንባ ይታጠብ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ቅኔያቸው የተያያዘው ከጽጌ ፆም ጋር ነበር። በግዕዝ “ጽጌ” ማለት አበባ ማለት ነው፤ ጥቅምት የአበባ ወቅት በመሆኑ። ሊቀ ማዕምራን አበባው ደግሞ አበባው ናቸው፤ ለባለቅኔዎች የተመቻቸ ስምና ወቅት! ይህስ እግዚአብሔር ያገጣጠመው ሌላ አጋጣሚ ይሆን? በእርግጥ ሰፋ አድርጎ ከታየ ለሊቀ ማዕምራን የቀብር ሥነ – ሥርዓት በተዋጣለት ሁኔታ መሳካትና ማማር ሌላ አጋጣሚም መጨመር ይቻል ነበር፤ አንባቢን የማያሰለች ቢሆን ኖሮ!

ይህ ሁሉ የማኅሌት፣ የፀሎተ – ፍትሃት፣ የአደራረስና የቅኔ ሥነ -ሥርዓት ቅዳሜ ከምሽቱ 3 ሰዓት ጀምሮ አስከ እሁድ ከቀኑ 5፡00 ድረስ ከተከናወነ በኋላ የሊቀ ማዕምራን አበባው ይግዛው የቀብር ቦታ በአቃቤ መንበሩ ፓትርያሪክ አቡነ ናትናኤል ተባርኮ የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ከቀኑ 5፡30 ላይ ተጠናቋል።  በቀብሩ ሥነ – ሥርዓት ወቅት ከዚህ ጽሑፍ መጨረሻ ላይ አብሮ የቀረበው  አጭር የሕይዎት ታሪካቸው ለሕዝቡ ታድሏል።

ሊቀ ማዕምራን አበባው ይገዛው አንደማንኛችንም አንድ ሰው ብቻ ሳይሆኑ በውስጡ በዙ የተለያዩ ዴፓርትመንቶችን እንዳቀፈ አንድ ተቋም ወይም አንድ ታላቅ ቤተ-መጻሕፍት ነበሩ ቢባል ተጋንኖ የተነገረ አይደለም። ምክንያቱም ይህንን ሃሳብ የሚጋሩ እጅግ ብዙ ሰዎች አሉና። በለቅሷቸው ላይም ከተለያዩ ሰዎች በተደጋጋሚ ይነሳ የነበረው “ከእንግዲህ ማነን እንጠይቅ? ቤተ – መጻሕፍታችን ተቃጠለ …” ወዘተ. የሚሉ ነበሩ።  እውነት ብለዋል! ምክንያቱም ሊቀ ማዕምራን አበባው ይግዛው ዘርፈ – ብዙ ዕውቀት የነበራቸው ታላቅ ምሑር ነበሩና!  ትናንት እነ ሎሬት ፀጋየ ገብረ ምድኅንን፣ እነ አርቲስት ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠን አና ክቡር ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌንና ሌሎች መሰል ምትክ የለሽ ልጆቿን ያጣችው እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ዛሬም ምትክ የማይገኝላቸውን የቤተክህነት ባለሙያ፣ ባለቅኔ፣ ገጣሚና እጅግ ሀገር ወዳድ ሰው በማጣቷ ሀዘኗ እጥፍ ድርብ ነው።

ሊቀ ማዕምራን አበባው ይግዛው በስማቸውና በተለያዩ የብዕር ስሞች ከሦስት መቶ በላይ ጽሑፎችን በስድ ንባብና በግጥም ጽፈው በተለያዩ መገናኛ ብዙሐን ለሕዝብ አቅርበዋል። ግጥሞቹን ቀንጨብ፣ ቀንጨብ እያደረግሁና ማን ማን በሚል የብዕር ስም ለአደባባይ እንደበቁ አምላክ የዚያ ሰው ይበለኝ እንጅ ወደፊት ይዠ ለመቅረብ ቃል እገባለሁ።

ኃያሉ አምላካችን ነብሳቸውን በገነት ቦታ ያኑርልን።

ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን እንዲሰጥልን እንለምናለን።

የቅኔው ባለሟል፣ የጥበብ ገበሬ፣
እንደወጣ ቀረ መርዶ ስሚ አገሬ።

የሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛው አጭር የሕይዎት ታሪክ፣

(ሚያዚያ 27/ 1933 – ጥቅምት 6/ 2005)

ሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛው ከአባታቸው ሙሉጌታ ይግዛው ድሌና ከእናታቸው ወይዘሮ ገላ ጎሹ፣ በደቡብ ጎንደር ክፍለ ሀገር፣ በደብረታቦር አውራጃ፣ በፋርጣ ወረዳ፣ ልዩ ስሙ አደንጎጥ በተባለ ቀበሌ፣ ሰላምኮ ጊዮርጊስ አካባቢ ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ተወለዱ።

ትምህርትና ዕድገት፦ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ፣ በደብረታቦር ከተማ ከታወቁት መምህራን አባ መርሻና መሪጌታ አዘዘ እንዲሁም ከታላቁ ሊቅ አለቃ ቀለመወርቅ ይማም ከፊደል እስከ ንባብ፣ ቃል ትምህርት እስከ ቁም ዜማ ተምረው፣ ከደጉ አባት ብፁዕ አቡነ ሚካኤል የጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ – ጳጳስ መዓረገ – ዲቁናን ተቀብለው በመንበረ ብርሃን እናቲቱ ማርያም ምሥጢር ከአዩ በኋላ፣ በመንበረ ልዑል ደብረታቦር መድኃኒዓለምና በመንበረ ንግሥት ልጅቱ ማርያም መደበኛ ዲያቆን በመሆን በምርጥ ዲያቆንነት ቀድሰዋል። በዲቁናው የሚያገለግሉትም የቃል ትምህርቱንና የዜማ ትምህርታቸውን በማጠናከር ነበር። በዚሁ ወቅት ከታወቁት የቁም ጽሕፈት ሊቅ መሪጌታ ካሤ ረታ የቁም ጽሕፈትን ሙያ በሚገባ ተምረዋል።

ከዚያም ከወላጆቻቸው ተሠውረው በጋይንት አውራጃ በስማዳ ወረዳ፣ ልዩ ስሙ ቃጨና ኢየሱስ ወደሚባለው ደብር ሂደው ከስመጥሩው የቅኔ መሪጌታ መምህር ዓለሙ ቅኔ ተቀኝተዋል። በዚያ በሚማሩበት ጊዜ በትምህርት ቤቱ የተስቦ በሽታ ገብቶ ብዙ ተማሪዎችን ሲገድል፣ እርሳቸው በጠና ቢታመሙም በእግዚአብሔር ቸርነት ተርፈው፣ በዚያው በስማዳ ሂዳሮ ማርያም ቤተክርስቲያን ቀሳ ወጥተው ነበር። ገመምተኛ ወደገበያ መውጣት የተለመደ ስለነበር አስታመው ያዳኗቸው ጓደኛቸው ዜና (በኋላ ቄስ ምናለ መላኩ) ወደ ኮሽ ገበያ ይዘዋቸው ወጥተው ሳለ ያዩዋቸው የደብረታቦር ነጋዴዎች ወሬውን ወደ ዘመድ ስላደረሱ፤ ቀደም ብለው ከመሪጌታ ዓለሙ የተቀኙት ትልቅ ወንድማቸው ሙሉጌታ መንግሥቴ ይግዛው በሂዳሮ ማርያም ስላገኟቸው፣ አብሯቸው ታምሞ ከዳነው ዘመዳቸው ቀለመወርቅ (አስተማሪ ጌትነት መርሻ) ጋር ይዘዋቸው ወደ ደብረታቦር ተመለሱ። ደብረታቦር ከተማ ሰኞ ገበያ ከሚገኘው የእናታቸው ቤት ትንሽ ሲያገግሙ እንደቆዩ ወደ ስማዳ መመለስ ስላልተፈቀደላቸው እዚያው በታላቁ ደብር ደብረታቦር ኢየሱስ ቅኔ ሲያስተምሩ ከነበሩት መሪጌታ አክሎግ ሲቀጻጽሉ ቆዩ። በኋላ ግን ጉልበታቸው ሲጠነክር፣ እንደገና ጠፍተው ወደስማዳ ሄዱ። በዚያም በቃጨና ኢየሱስ ከመሪጌታ ዓለሙ ቅኔ በሚነግሩበት ጊዜ እንዳጋጣሚ ታላቁ የቅኔ መምህር አለቃ ጌጡ ተሰማ (የመሪጌታ ዓለሙ አስተማሪ የነበሩ) ከደብረታቦር ወደ ደብረ ዕንቁ ሲሄዱ በእንግድነት  አርፈው ስለነበረ፣ “ይኸንን ልጅ ለእኔ ስጠኝ” ብለው ወደ ደብረ ዕንቁ ይዘዋቸው ሄዱ። በዚያም የተቀኙትን ቅኔ ከነአግባቡ ለሁለት ዓመታት ካጠናከሩ በኋላ፣ ለዘራፊነት በቅተው፣ የመጽሐፈ – ነገሥትና የቅዳሴ ማርያምን ትርጉም እንዲሁም አቡሻክርን ከቀጸሉ በኋላ አቋቋም ለመማር ወደ ትውልድ ደብራቸው ተመለሱ።

ወደ አቋቋም ቤት ከመሄዳቸውም በፊት የዜማ ትምህርታቸውን ለማጠናከር ወደ ታዋቂው የዜማ መምህር መሪጌታ ጀንበር አዛውር ኪዳነ – ምሕረት ሄደው ጾመድጓውን ከላልሰው ቁም ዜማውን እስከ ምዕራፍ ካጠናቀቁ በኋላ፣ ወደ እብናት ደብር ሚካኤል ከእነ መላከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን ጋር አቋቋም ለመማር ቢሞክሩ፣ ሕፃን ነህ ብለው መለሷቸው። የተክሌን አቋቋም ለመማር የነበራቸው ተስፋ በዚሁ ስለታገደባቸው ሃሳባቸው ተለወጠ።

ለትምህርት የነበራቸው ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ወዲያውኑ ጊዜ ሳያጠፉ፣ እንደጓደኞቻቸው ዘመናዊ ትምህርት ለመማር ወሰኑ። አስኳላም ለመግባት ዘመዶቻቸው ደጋግመው ስለከለከሏቸው ከእናታቸው ጠፍተው በእግራቸው ዘጠኝ ቀን ተጉዘው አዲስ አበባ ገቡ። የተጓዙት ከአክስታቸው ባል አቶ አበባየሁ ደስታ ከሚባሉ አዲሰ አበባ ሙግት ከነበረባቸው ሰው ጋር ነበር። ከአንዳ ቤት አባይ አፋፍ እስኪደርሱ  ድረስ ሰውየውን እየተደበቁ ነው የተከተሏቸው። ሊቀ ማእምራን አበባው ይህንን ታሪክ ሲናገሩ ያፈዝዙ ነበር።

የካቲት 7 ቀን ሰኞ 1947 ዓ.ም. ከደብረታቦር ከተማ ተነሥተው የካቲት 16 ቀን 1947 ዓ.ም. እንጦጦ ኪዳነ ምሕረት ደረሱ። በዚያም ክብረ በዓል ስለነበረ ከዚያው ቀማምሰው ሳንቲሞችንም ለማምነው፣ ወደ መናገሻ ገነተ-ጽጌ ጊዮርጊስ ደረሱና ከጥንት መምህራቸው አለቃ ቀለመወርቅ ይማም ጋር ተገናኝተው በዚያው በሕብስተ ሰናፔ  ትምህርት ቤት በረንዳ ተጠግተው አቋቋም እየቀጸሉ የዘመናዊውን ትምህርት ደጅ – ጥናት ቀጠሉ። ለአምስት ወራትም በገዳም ሠፈር በቆሎ ተማሪነት ለምነው እየበሉና ከጊዮርጊስም መሐራ እየተሳተፉ ከቆዩ በኋላ በብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ መልካም ፈቃድ በቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ት/ቤት፣ ኮልፌ፣ የተሥፈኝነት ቦታ አገኙ። የተስፈኝነት ቦታ ማለት መደበኛ ቦታ እስኪገኝ ጊዜ ድረስ የተራረፈውን ፍርፋሪ እየበሉ ደጅ መጥናት ማለት ነው። ትምህርት ግን ይፈቀዳል። ወደ ኮልፌ የተላኩት በሐምሌ ወር ስለነበረ ትምህርት ቤት ዝግ ነበር። ሆኖም ታላቁ የትምህርት ሙያ አክባሪ ሰው አቶ በትረ – ጽድቅ ካሣ በተሰጣቸው አደራ መሠረት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሙሉ የአዳሪነት ቦታ አግኝተውላቸው መደበኛ ተማሪ ሆኑ።

መሥከረም ወር 1948 ዓ.ም. አንደኛ ክፍል ገብተው ለዐራት ዓመታት የሚሰጠውን ትምህርት አንደኛ አንደኛ እየወጡ በሁለት ዓመታት በማጠናቀቅ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ለመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪነት ኮርስ ተፈትነው ከብዙ ሊቃውንት መካከል በአንደኛነት አለፉ። ከዚያም የመጀመሪያውን መንፈቀ ትምህርት ብቻ እንደተከታተሉ አቶ ገብረ ኢየሱስ የሚባሉ አዳሪ ተማሪ ለውጠዋቸውና በመደበኛ አዳሪ ተማሪነት መደበኛውን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቀጥለው አሁንም የዐራቱን ዓመት ትምህርት በሁለት ዓመታት በማጠናቀቅ ድርብ ዕድገት አያገኙ በ1951 ዓ.ም. ብሔራዊውን የ8ኛ ክፍል ፈተና በአንደኛነት በማጠናቀቅ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተመደበው ዐራት ዓመት አጠናቅቀው ማትሪክ አለፉ። በሁለተኛው ደረጃ ትምህርትም ቢሆን ድርብ ዕድገት ስለማይሰጥ ነው እንጅ በመጀመሪያው ግማሽ ዓመትም ሆነ በዓመቱ መጨረሻም አንደኛ እየወጡ ትምህርቱን ጠቅጥቀውት ነበር። ዐራት ዓመታት በአንደኛ ደረጃ፣ ዐራት ዓመታት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ፣ በየዓመቱ መጨረሻ አንደኛ አንደኛ ይወጡ ስለነበር ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ 8 ጊዜ ሽልማት ተቀብለዋል።

በአንደኛ ደረጃም ሆነ በሁለተኛ ደረጃ በሚማሩበት ጊዜ፣ የሥዕል፣ የክርክር፣ የእስካውት ክበብ አባል በመሆን አገልግለዋል። በኮሌጅ የተቋቋመው የሰንበት ት/ቤትና የወንጌል መልዕክተኞች ማኅበርም አባል በመሆን ሠርተዋል። የሥዕል፣ የሥነ-ጽሑፍ፣ የቅኔና የግጥም ተሰጥዖዋቸውን በአደባባይ አስመሥከረዋል። በቁም ጽሕፈት ሙያቸውም ተመርጠው በቅድስት ሥላሴ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ሠራተኞችን አስተምረዋል። በጊዜው የተማሪዎች ዲንና አስተማሪ የነበሩትን አቶ ገበረሥላሴን ለዚህ ዓይነት ሥራ፣ ዕቅድና አመራር በጣም ያደንቋቸው ነበር።

በ1956 ዓ.ም. 12ኛ ክፍልን አጠናቅቀው በዩኒቨርስቲው ከተመዘገቡ በኋላ፣ ደኃ እናቴን እረዳለሁ በማለት በፍርድ ሚኒስቴር ተቀጥረው አገልግለዋል። በኋላም ወደ ግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ልዩ ካቢኔ መንፈሳዊ ክፍል ተዛውረው አገልግለዋል። በሥራ ላይ በነበሩባቸውም ሁለት ዓመታት በአ.አ. ዩኒቨርስቲ በማታው የትምህርት ክፍል ተመዝግበው የአንደኛ ዓመት እንግሊዝኛና አማርኛ  ትምህርታቸውን አጠናቅቀዋል።

በ1957 ዓ.ም. ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀ. ኃ. ሥ. ሮማንያን በኦፊሴል በጎበኙበት ወቅት የሮማንያን ፓትርያርክ አባ ጁስቲኒያን በመንበረ ፓትርያርካቸው ጎብኝተው ነበር። ታዲያ በዚሁ አጋጣሚ ለአምስት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ነፃ የመንፈሳዊ ትምህርት ዕድል ስለሰጡዋቸው ጃንሆይ ከጉብኝት እንደተመለሱ አምስት ወጣቶች ተመርጠው እንዲላኩ ሲወሰን ዕድል ከገጠማቸው አንዱ ሊቀ ማእምራን አበባው ነበሩ። በዚሁም መሠረት ለ5 ዓመታት በሮማኒያ የቴኦሎጂ ዩኒቨርሰቲ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ተምረው በ1961 ዓ.ም. በመዓርግ ተመርቀው ለዶክትሬት ተመዝገበው ነበር። ከመመረቃቸው አምስት ወራት በፊት የሮማኒያ ፓትርያርክ አባ ጁስቲኒያን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ በግርማዊ ን.ነ. ቀ. ኃ. ሥ. ተጋብዘው እንደ አውሮፓዊያን ዘመን አቆጣጠር በጥር ወር 1969 ዓ.ም. ወደ አ.አ. መጥተው ነበር። የጥምቀትንና የቃና ዘገሊላን በዓላት ተከታትለዋል፤ ለክብራቸው በተዘጋጀውም ግብዣና የሽልማት ፕሮግራም ከግርማዊ ን.ነ. ጋር ለብዙ ሥዓታት ተገናኝተው ተወያይተዋል። ታዲያ ለዚህ ጉብኝት አስተርጓሚ ሆነው የመጡት ሊቀ ማእምራን አበባው ስለነበሩ ፓትርያርኩ በተገኙባቸው ጉብኝቶች ሁሉ አልተለዩም። በቤተክህነትም ሆነ በቤተመንግሥት ለተደረገላቸው አቀባበልና መስተንግዶ ከሮማንያንኛ ወደ አማርኛ፣ ከአማርኛ ወደ ሮማንያንኛ አስተርጓሚ ሆነው አገልግለዋል። ጃንሆይም እንግዶችን ሲሸልሙ ሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛውንም ሸልመዋቸዋል።

ትምህርታቸውን ጨርሰው እንደተመለሱ ወደ ትምህርት መርጠው በላኳቸው የትናንቱ ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ የዛሬው ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ አማካይነት ወደ ጃንሆይ ቀርበው ነበር። ለዶክትሬት እንዲቀጥሉ የተጻፈላቸውንም ደብዳቤ ለጃንሆይ አቅርበው ቀጣዩን ትምህርት ለመማር እንዲፈቀድላቸው ግርማዊ ጃንሆይን ጠየቁ። ጃንሆይ ግን አንዳንድ ጥያቄዎችን አንስተው ከመለሱላቸው በኋላ፣ “በተማርከው ትምህርት ከሊቀ ሥልጣናት ጋር ሁንና አገልግል።” ስላሏቸው የዶክትሬቱን ትምህርት ሳይቀጥሉ ቀሩ።

ከዚያም መጀመሪያ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በዋና ጸሐፊነት፣ ቀጥሎም በካቴድራሉ ሥር በሚካሄደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ድርጅት በዳይሬክተርነት፣ በሰባኪነትና በሥነ ጽሑፍ አራሚነት አገልግለዋለ።

ቀጥሎም  የአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ አብያተ መጻሕፍት ለምሩቃን ሥራ ፈላጊዎች ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድረው አንደኛ በመውጣት በዩኒቨርሰቲው ቤተ መጻሕፍት ልዩ ልዩ የሥራ ዘርፎች እየተመደቡ አገልግለዋል። ልዩ ልዩ ሥልጠናም ወስደዋል። የቤተ መጻሕፍቱ ኮሚሽንም አባል ነበሩ።

በአጣቃላይ አገልግሎታቸው ሲታይ፡

  • በቤተ ክህነት የስበከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊነት፣

  • በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ቤተ መጻሕፍት፣

  • በደርግ ጽ/ቤት በፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ ቡድን በትውስት፣

  • በጎንደር ክፍለ ሀገር የሰላም ልዑክነት፣ የጎንደር ከንቲቫነትና በኋላም የክፍለ ሀገሩ ምክትል አስተዳዳሪነት፣ (ለ5 ዓመታት)፣

  • የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራአስኪያጅነት (7 ዓመታት)፣

  • በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሬስና ማስታዎቂያ መምሪያ ተ/ኃላፊነት (ለ2 ዓመታት)፣

  • በስዊድን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሚኒስትር ካውንስለርነት፣

  • በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ መንግሥትና የገዳማቱ ንብረት በጉዳይ ፈጻሚነት፣ በፕሮቶኮል እየተሾሙና እየተመደቡ ቅን አገልግሎታቸውን አበርክተዋል።

በብዙ ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ ስብሰባዎች እየተወከሉ ንቁ ተሣትፎ አድርገዋል። በሀገር ውስጥ የአገር አቀፍ የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል፣ የሀገር አቀፍ የዕርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል፣ የኢየሩሳሌም ጉዳይ የቴክኒክና የሚኒስትሮች ኮሚቴ አባል፣ የኢትዮጵያና የሶቪየት ኅብረት የወዳጅነት ኮሚቴ አባል፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ወዘተ. በመሆን የሚጠበቅባቸውን ተልዕኮ ተወጥተዋል። ከሙያቸው አንፃር አንዳንድ ሃይማኖትን፣ ባህልንና ሀገርን የሚመለከቱ ጽሑፎችንና መግለጫዎችን በቴሌቪዥንና በራዲዮ በተደጋጋሚ አቅርበዋል።

የሙዚቃው ንጉሥ ዶ/ር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ያላቀነቀነበት የኢትዮጵያ ጉዳይ የለም እንደሚባለው ሁሉ፣ የቅኔ ባለሙያው፣ አንደበተ ርቱዑና ሊቁ ሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛውም ያልጻፉበትና ያልተቀኙበት የኢትዮጵያ ጉዳይና የሕዝብ ብሦት የለም ቢባል ተጋንኖ የተገለፀ አይደለም።

በአጠቃላይ ሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛው የኢትዮጵያን ሕዝብ ታሪክ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ሕይዎት የሚዳስሱ ከሦስት መቶ በላይ የሚሆኑ ጽሑፎችን በስድ ንባብና በግጥም ያበረከቱ ታላቅ የሥነ-ጽሑፍ ሰው ነበሩ። አብዛኛዎቹ ሥራዎቻቸውም ታትመዋል።

ሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛው፣ የግራዝማች መንገሻ ደለሉንና የወይዘሮ ተዋበች ሠይፉን ልጅ ወ/ት ሐረገ ወይን መንገሻን በተክሊልና በቁርባን ጥር 4 ቀን 1967 ዓ.ም. አግብተው ሦስት ሴቶችንና አንድ ወንድ ልጅ ያፈሩ ሲሆን 2 የልጅ ልጆችም ለማየት ታድለዋል። ልጆቻቸውም ተምረው ለሥራ በቅተዋል።

ከሰኔ ወር 1984 ዓ.ም. ጀምሮ ከነመላው ቤተሰባቸው ከእየሩሳሌም ወደ ታላቋ ብሪታኒያ በማምራት ሕይዎታቸው እስካለፈበት ጥቅምት 6 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ በዚያው አሳልፈዋል።

ሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛው በተፈጥሯቸው ብልህ፣ ቅን፣ ትሁት፣ ርሕሩህና እጅግ በጣም ለጋስ ሰው ነበሩ። በዘመዶቻቸው፣ በጓደኞቻቸውም ሆነ በሥራ አለቆቻቸው የተወደዱና የተከበሩ ሰው ነበሩ። ከማንም ጋር በቀላሉ ወዳጅነትን የሚፈጥሩ፣ ግልጽ፣ ተግባቢና ሰውን አክባሪ ነበሩ። ጨዋታ የሚወዱና ጨዋታቸውም የሚያምርላቸው፣ ንግግራቸው ሁሉ በቅኔ፣ በምሳሌያዊ አባባልና በዘይቤ የበለፀገ ነበር። አንዳንድ ንግግራቸው እንደ አለቃ ገብረ ሐና ዘይቤ ለሰሚው የሚገባው ዘግይቶ ነው።

የሊቀ ማእምራን አበባው ሕይዎትና ሙያዊ ብቃት ዘርፈ ብዙ ነበር።  የሃይማኖትም የፖለቲካም ሰው ነበሩ። ሁለቱንም በሚገባ የተካኑበት ከመሆናቸውም በላይ ጥሩ አድርገውም ሠርተውበታል። በቅርብ የሚያውቋቸው በሁለቱም በኩል ያላቸውን ሙያና ስጦታ ያደንቁላቸዋል። ሲከራከሩ ነጥብ አያሳልፉም። አሳማኝ ነጥቦችን መሠንዘር የሚችሉ፣ በሀገር ጉዳይ ላይ በማያምኑበት ሰውን ለማስደሰት ሲሉ ብቻ ከቆሙበት ዓላማ ወይም ከያዙት አቋም ፍፁም ፍንክች የማይሉ እና እጅግ ሲበዛ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ነበሩ።

ባለቅኔውና ገጣሚው ሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛው እጅግ የሚወዱትን ሥነ – ጽሑፍም ሆነ ይህችን ዓለም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተሰናበቱት ሆስፒታል ውስጥ  የሕይዎታቸው የመጨረሻ ጠርዝ ላይ እያሉ በቋጠሯት በዚህች የመጨረሻ መልዕክት ነው፦

ሊቀ ማእምራን፣ የደብረታቦሩ፣
ከዚህ አርፏልና አትነጋገሩ።
ንግግር ሰልችቷል፣ መስማትም ታክቶታል፣
በቁመናው ሳለ ሁሉንም ጠግቦታል።
ጽሑፍ ንግግሩ ቅኔ መቀኘቱ፣
ተሰጥዎው ነበረ ከሕፃንነቱ

ፈጣሪ አምላካችን ነብሳቸውን በገነት ያኑርልን።
ለባለቤታቸው፣ ለልጆቻቸውና ለመላ ተሰባቸውም
አምላክ መጽናናቱን ይስጥልን።

 ለካስ ለዚህ ነበር

(የሐዘን እንጉርጉሮ ከውድ ባለቤታቸው ከወ/ሮ ሐረገወይን መንገሻ)

አሁንስ ልናገር የልቤን አውጥቼ፣
ዘመኑንም ላስታውስ ሁሉን እረስቼ፣
ባለቤት የሚሉትን ቃል ከአእምሮየ አንስቼ፣
አባትም እናትም፣ እህትም ወንድምም፣
መሆንክን አምኘ በአንተ ተመክቼ፣
በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አንተን ተሰጥቼ፣
የሕይዎቴን ተስፋ የትዳሬን ዋልታ ምሠሶን መሥርቼ፣
ሁሉን ያየሁበት ቤተሰብ አግኝቼ፣
አቢ ፍቀድልኝ አሁንስ ልናገር የጥንቱን አውጥቼ።

አቀበት ቁልቁለት ጋራ ሸንተረሩን፣ አጋሙን ቀጋውን ውሃ ጥም ራቡን፣ ሁሉን ተቋቁመህ፣
በጠንካራ ስሜት በተስፋ ተጉዘህ፣
የአባይን በርሃ አቆራርጠህ ወጥተህ፣
እህል ውሃ ሆኖ ከሰሜኑ ክፍል መሃል ሀገር ዘልቀህ፣
ከዱር አራዊቱ ከሽፍታ ተታግለህ፣
አእምሮህን በዕውቀት በትምህርት አዳብረህ፣
በቅድስት ሥላሴ ሞገስን አግኝተህ፣
በተዋህዶ እምነት ትህትናን ተላብሰህ፣
ቋንቋውና ባህል ዘሩም ሳይወስንህ፣
ኢትዮጵያዊነትን ስሜትህን ሞልተህ፣
የቃል-ኪዳን ሚስጥር ከልቤ አስቀምጠህ፣
የጎንደርን ማተብ ካንገቴ ላይ አሥረህ፣
“ከሞት በስተቀረ ካንቺ የሚለየኝ ከቶ የለም” ብለህ፣
መሃላውን ሁሉ ሥርዓቱን ጠብቀህ፣
በጣም ይደንቀኛል ቃልህን ማክበርህ፣
በጣም ይገርመኛል የተናገርከውን በተግባር መግለፅህ፣
ማተብክን ጠብቀህ ለዚች ቀን መብቃትህ፣
“ሐረግ፣ ሐረግ” እያልክ ትተኸኝ መሄድህ፣
አበባ እንደሆንከኝ በምድር ላይ ሳለህ፣
እናት ቤተክርስቲያን ወደ ሰማይ ስትሄድ እርሱዋ ትጠብቅህ፣
በአብርሃም በይሥሐቅ በያዕቆብ ታቁምህ፣
አገልግሎትህን ጌታ ይቁጠርልህ፣
መንግሥተ – ሰማያትን አምላክህ ያድልህ።

Comments (2)

  • MiMi

    Telqe abate new yatanew. Le hulu arya yemihonu. Ye Ethiopia amlake nefsachewen yemare.

    Mimi

    Reply
  • Hailegnaw Habtemichael

    እጅግ የተከበሩና ውድ የኢትዮጵያ ልጅ የሆኑትን ታላቁ አባታችንን ሊቀማእምራን አበባ ይግዛውን በሞት መነጠቃችን እጅግ ቢያሳዝነንም በህይወታችን ዘመን ሁሉ የምንገለገልበትን ዕውቀት ትተውልን በማለፋቸው ስማቸውና መልካም ምግባራቸው በእኛ በኢትዮጵያ ኦርኦዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጆች ልብ ውስጥ ምንጊዜም ይኖራል : : እኛም የአባታችንን ፈለግ ተከትለን የመሄድ ግዴታችንን አንዘነጋውም : : የኢትዮጵያ ዓምላክ የአባታችንን ነፍስ በመንግሥተ ሰማያት ያኑርልን : : አሜን !

    Reply

Leave a Comment

© 2007-2012 Abbay Media ‘The Ethiopian Information Bank’

Scroll to top