የኢትዮጵያ ባንኮች፣ ለወለድ ወይስ ለግርዛት? የአባይ ሚድያ ሳምንታዊ ጦማር አስማተኛ ዝምታን ያውቅበታል፡፡ ሥራውን የሚሰራው በዝምታ ነው፡፡ ጉድ የሚያሰኙ ምትአቶችን በዝምታው ሥር ተጠልሎ ያከናውናል፡፡ ሐበሻም እንዲሁ ነው፤ አስማት ይችልበታል፡፡ ሕይወቱ በአስማት የተሞላ ነው፡፡ ኑሮው በተአምር የታጀበ ነው፡፡ ለሌሎች የሰው ዘሮች በፍጹም የማይቻሉ የሚመስሉ – ከሰማይ ስባሪ በላይ የሚከብዱ ችግሮችን በዝምታ ይችላቸዋል፡፡ የቱንም ያህል ቢከብደው ለራሱ ያጉተመትም ይሆናል እንጂ “ከበደኝ” ብሎ አይቃወምም፡፡ የለም! የኢትዮጵያ ሕዝብ በተስፋ ተሞልቶ መዋል መተኛት ይችልበታል፡፡ ግን ይሄ ትዕግስቱ እስከመቼ እንደሚጸና አምላኩ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ የሕዝቡን ዝምታ እንደፍራቻ ለመቁጠር ማመንታት ያልፈጠረባቸው ብዙ ይኖራሉ፡፡ ዝምታውን እንደ”ምቾት” መውሰድ ግን ተሳዳቢነትና አለማወቅ ነው፡፡ ከየት የመጣ ምቾት ነው? … ምቾትን ለሕዝብ ያከፋፈለ መንግስት አለ እንዴ በሀገሩ? … የሚበላው እንጀራ ጠፍቷልኮ! ቢገኝም ክብሩ ከወርቅጋ አንድ ሆኗል፡፡ ለዛውም ለጣት አሻራ ጋር ተጣብቆ አልላቀቅ የሚል እንጀራ፡፡ የዋጋ ግሽበት “ኑሮው ተወዷል፤ መቼም የምግብ ዋጋውን ታውቁታላችሁ!” ብትባሉ አዎ እንዳትሉ፡፡ እመኑኝ አታውቁትም፡፡ የሚታወቀውኮ ዋጋው አርፎ አንድ ቦታ ቢቀመጥ ነበር፡፡ እስስት የሆነ ዋጋ እንዴት ይታወቃል? ቀጣፊ ሬድዮ በገመተላችሁ መሰረት ብር ይዛችሁ ለገበያ ዉጡና ዋጋውን ጠይቁ፡፡ ዋጋው መዝሙሩን ለውጧል፡፡ ቅናሽ ለማግኘት ቢሽከረከሩም ለሁለት ዓመት የገዙት ጫማ በአራተኛው ወር ይገነጠላል እንጂ ቅናሽ የለም፡፡ የመጀመሪያው ነጋዴ ይሻለኛል ብለው ሲመለሱ መሬት የነበረው ዋጋ ጣሪያ ላይ ወጥቶ ይጠብቆታል፡፡ እንዴት ያለ ከፍታ ዘላይ ነው ንግዱ? እና የዘንድሮ ገበያ ዋጋ አይታወቅም! ተመን የሚያወጣው ነጋዴው ሳይሆን የሚነፍሰው ነፋስ ይመስለኛል፡፡ ሰው እንዴት ይሄን ያህል በሌሎች ላይ ይጨክናል?! ሰው ሲፈጠር የጭካኔ ባህሪ የለውም፡፡ ለሰው ጭካኔን የሚያስተምሩት ሰዎች ናቸው፡፡ የራሳቸውን ሐብትና ንብረት ለማደርጀት ሲሉ የኢትዮጵያን የንግድ ሥርዓት ወጥረው የያዙት “ብልጥ” ባለስልጣናት ቁጥራቸው ከስታቲስክስ ዕውቀት በላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሀብት እንደአድባር አነባበሮ ሸንሽነው የተከፋፈሉት እጅግ ጥቂቶች ናቸው ፡፡ ቀሪው ሕዝብ አድባር መኖሩን እንኳ ረስቷል፡፡ ግንቦት 20 የሚባል የ”ትንሳኤ” በዓል ከመጣ ጀምሮ ግንቦት ልደታን ማክበር ቅንጦት ሆኗል፡፡ ሕዝቡ የዋጋን መውረድ መናፈቅ ትቷል፡፡ ዋጋ እንደጻድቃን ያረገባት ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ የኢትዮጵያ ነፋሻማው ውብ አየር ተለውጦ ሲጋራ የሚለኩስ ጸሐይ የነገሰው ለምንድነው? ምናልባት ዋጋ ወደሰማይ ሲያርግ የኦዞንን ንጣፍ /ozon layer/ ቀዶት ይሆናል፡፡ አሁን አሁን ሕዝቡ የዋጋን መውረድ መናፈቅ ትቶ “የዛሬው ዋጋ ከነገው ዋጋ ይቀንሳል” እያለ መጽናናት ጀምሯል፡፡ በሕንድ ጥቂት ግዛቶች የሚኖሩ ዜጎች የተቃውሞ ሰልፍ መውጣታቸውን እንደኔ ወሬ ሳትሰሙ አልቀራችሁም፡፡ ተቃዉሟቸውን የቀሰቀሰው የዋጋ ግሽበቱ 7% /ሰባት በመቶ/ በመጨመሩ እንደሆነ ስሰማ ለራሳችን አዘንኩ፡፡ በኢትዮጵያ “የተከሰተው” የዋጋ ግሽበት … /የተከሰተው ከማለት ይልቅ “የተፈጠረው” ማለቱ የበለጠ እውነቱን ይገልጸዋል/ …ከሕንድ ግሽበት ከሶስት እጥፍ በላይ ነው፡፡ 25 በመቶ ያደገው የሀገሬ ግሽበት በርዝመት መለኪያ ተለውጦ ልኩ ቢታወቅ ኖሮ ቁመቱ ከአራዳ ፎቅ እንደሚበልጥ አያጠራጥርም፡፡ ይሄን ያህል ሲንቀዋለል ሕዝቡ በዝምታ አስማታዊ ኑሮውን እንደቀጠለ ግልጽ ነው፡፡ ግን መንግስት የት ሄዶ ነበር? የግሽበቱ ከፍታ በየቀኑ እየጨመረ ሰማይ ሲደርስ መንግስት ምን እያደረገ ነበር? በግንባታ ላይ እንዳለ ፎቅ በፈገግታ ሲያየው የከረመ ነው የሚመስለው፡፡ ፎቁን ብቻ አንጋጦ የሚያይ መንግስት ከሥር የሚርመሰመሱትን ድሃ ዜጎች ማስተዋል አቅቶታል፡፡ ያን የግሽበት ፎቅ ለመገንባት የሚያቦካው ሲሚንቶ ውስጥ ደቃቅ አሸዋ የመሰሉ ድሆች አሉ፡፡ ለነሱ የዋጋ ግሽበቱ ልክ እንደ “ደም ብዛት” በሽታ አስከፊ ነው፡፡ ቢሆንም የነዚህ ሕመምተኞች ሕይወት ትኩረት አልተሰጠውም፤ የእነሱ ዝምታ ተርጓሚ አላገኘም፡፡ የድሃውን ዝምታ በቅጡ መተርጎም ያልቻለ መንግስት ደግሞ የግሽበቱ ቁመት የቱንም ያክል ቢመዘዝ አያሰጋውም፡፡ የመንግስት ስጋት ዝምታ ሳይሆን ድምጽ ነው፡፡ የተቃውሞ ድምጽ! የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን አስማተኛ ነው፡፡ አስማተኛ ዝምታን ያውቅበታል፡፡ ሥራውን የሚሰራው በዝምታ ነው፡፡ ጉድ የሚያሰኙ ምትአቶችን በዝምታው ሥር ተጠልሎ ያከናውናል፡፡ የባንክ ወለድ? “በመጠኑ” ለመኖር የሚፍጨረጨረውን ኢትዮጵያዊ ከዋጋ ግሽበቱ ጎን ሆኖ የሚያሰቃየው ሌላ ችግር የባንክ ወለድ ማነስ ነው፡፡ አሁን የበፊቱ በሽታቸው ላይ “ደም ማነስ” ተጨመረ ማለት ነው፡፡ ባንኮች ከ5 በመቶ ወለድ በላይ ለመክፈል ፍጹም አቅም እንደሌላቸው ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ ያም ሆኖ በባንክ አሰራር ላይ ዝርዝር መረጃ የሌለው ብዙሐኑ ወገን ገንዘቡን ወደባንክ ከመውሰድ ወደኋላ አላለም፡፡ የባንክ ጥቅም ገንዘባችን ዓመቱ መጨረሻ ላይ 5 በመቶ እንዲወልድልን ነበር፡፡ ለምሳሌ ዛሬ ባንክ ያስቀመጥነው መቶ ብር የዛሬ ዓመት ስናወጣው 105 ብር ይሆንልናል፡፡ በርግጥ ቆጥረን ስንረከው ብራችን 5 በመቶ ጨምሯል፡፡ ግን አስታውሱ! በ105 ብሩ ምን ልንገዛ እንችላለን? የዋጋ ግሽበቱ ከ25 በመቶ በላይ ጨምሯል፡፡ ይሄ ማለት የዛሬ ዓመት 100 ብር ልንገዛው የምንችለው ዕቃ አሁን 125 ብር ገብቷል እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህ ያን ዕቃ በ125 ብር ለመግዛት ከባንክ ካወጣነው 105 ብር ላይ ሃያ ብሮች ከኪሳችን ለመጨመር እንገደዳለን፡፡ አሁን፣ ብር ባንክ የሚገባው ለወለድ ሳይሆን ለግርዛት ነው፡፡ ዛሬ መቶ ብር ባንክ ቢያስቀምጡ ባመቱ ሲያወጡት 85 ብር ሆኖ እንደሚያወጡት ተረዱኝ? በሌላ አነጋገር ባንክ የገባ ብር የነፈሰበት ሲሚንቶ እንደማለት ነው፡፡ ባንኮች አትራፊ ሆነው እንዲቀጥሉ ሕዝቡ ባንክ ላስቀመጠው ገንዘቡ ከገዛ ኪሱ እያወጣ ለአንዲት ብር 20 ሳንቲሞች መደጎም አለበት፡፡ ስለዚህ ለክፉ ጊዜ ብር ባንክ አስቀምጦ መዝናናት አሁን በኢትዮጵያ የለም፡፡ አሁን ሕዝቡን ከክፉ ጊዜ በላይ የሚያስፈራው የባንኮች ክፉነት ነው፡፡ ኑሮን በባንክ ወለድ መደጎም የሚባለው ሐሳብ ከሀገር ከተሰደደ ቆይቷል፡፡ ሕዝባችን የሚደገፈው ምርኩዝ እያጣ ነው፡፡ ከዘራ እና መቋሚያ ያለው ሰው ወፍጮ ቤት እንዳለው መቆጠር ጀምሯል፡፡ በአንድ በኩል የዋጋ ግሽበት፣ በሌላ ወገን በኪሳራ የሰከረ የባንክ ወለድ፤ የሕዝቡን ዝምታ እየተፈታተነው ነው፡፡ የቦንድ ግዢ ሌላም ፈተና አለበት ሕዝቡ፤ ማምለጫ ቀዳዳ የሌለው ፈተና፡፡ “የውዴታ ግዴታ” ይሉታል ሰባኪያኑ፡፡ የአባይ ግድብ በኢትዮጵያውያን ወጪ እንዲገነባ ዕቅድ ተይዟል፡፡ የእያንዳንዱ ግለሰብም ኪስ ተይዟል፡፡ ከነወለዱ ወይም ከወለድ ነጻ ቦንድ መግዛት የዜጎች ሁሉ ድርሻ ተደርጎ ተወስኗል፡፡ ሁለት ያለው አንዱን ቢሰጥና አንድ ብቻ ያለው ከሰቀቀን ቢያመልጥ ጥሩ ነበር፡፡ በቦንድ ግዢ ጉዳይ ላይ ግን ሁሉም እንዳለው ተደርጎ ነው የተወሰደው፡፡ በዋጋ ግሽበት እና በአክሳሪ የባንክ ወለድ በመንገዳገድ ላይ ያለን ሕዝብ በቦንድ ግዢ ማስገደድ አንዲት ጸጉሩን ስቦ እንደመጣል ይቆጠራል፡፡ እንደሚታወቀው አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ሠራተኞች በመንግስት ሥር ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ በተጽእኖ ለመታሰር በቂ ቦታ ነው፡፡ ጥቂቶች በምክንያት የተቀበሉትን ጥሪ ብዙዎች በዝምታ ይቀበሉታል፡፡ አሁን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ከማለታችን በፊት ስለደም ማነስና መብዛት ማውራታችን አይረሳም፡፡ የባለፈው ዓመት ሠራተኞች ሁሉ የአንድ ወር ደሞዛቸውን በ12 ወራት ተከፍሎ በሚያልቅ ክፍያ ቦንድ መግዛታቸው ይታወሳል፡፡ ለዚሁ ግዢ ሰሞኑን የቦንድ ወረቀት በየመስሪያ ቤቱ ላሉ ገዢዎች እየተከፈለ ነው ፡፡ በርግጥ ገዢው ቦንዱን ወደጥሬ ብር የሚለውጠው ከ2007 ዓ.ም በኋላ ነው፡፡ “ከነወለዱ ይከፈልሃል” የተባለው 1.000 ብር ከሦስት ዓመታት በኋላ ሲመጣ ድስት ውስጥ የገባ ጎመን ይሆናል፡፡ “ባልሽ ሞቶብሽ፣ ምጥሽ መጥቶብሽ፣ ጉንዳን ገብቶብሽ፣ መብራት ጠፍቶብሽ” ይላችዋል ምሳሌው፡፡ የባለፈውስ አለፈ አንበል፤ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ቦንድ እንዲገዛበት የተበየነበት ደሞዙስ? ያለፈውን ብድር መልሶ ሳይሰጥ ድጋሚ ብድር የሚጠይቅ ማነው? ባይወልድለት እንኳ ዋናውን ብር መልሶ ማግኘት ያልቻለው ሕዝብ ድጋሚ ደሞዙን ሲሰጥ ለኑሮው ምን ዋስትና ይዞ ነው? … በነጻ መታከሚያ ሆስፒታል የለውም፤ የኪሱ አቅም እንኳን ለመድሐኒት መግዣ ሆስፒታል ለሚያደርሰው ታክሲም አይበቃ፡፡ መሶቡ ባዶ ሆኖበት ድንጋይ ነክሶ ከቤቱ ይወጣል፡፡ መንገድ ላይ ካገኘው ጎስቋላ መሰሉ ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ ታዲያ “ተመችቶሃል ባክህ” መባባላቸው አይቀር ይሆናል፡፡ ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ ችግርን ይንቁታል፡፡ ቢሆንም የኢትዮጵያ ሕዝብ አስማተኛ ነው፡፡ አስማተኛ ዝምታን ያውቅበታል፡፡ ሥራውን የሚሰራው በዝምታ ነው፡፡ ጉድ የሚያሰኙ ምትአቶችን በዝምታው ሥር ተጠልሎ ያከናውናል!! Recommend on Facebook Tweet about it Subscribe to the comments on this post Print for later Bookmark in Browser Tell a friend ‹ Previous Next › Related posts የወያኔን ሰላዮችን ከውጭ አለም ማጽዳት እንደ መከላከያ ሁሉ ኢትዮ ቴሌኮምም ጠ /ሚያችን ሃይለማርያም ራሳቸው እሰረኛ “እስረኛ የለም” ይላሉ ሰብአዊ መብትና: መንግሥታዊ ግፊት በኢትዮጵያ (2012) Leave a Comment Click here to cancel reply. Name* Email* Website Submit Comment