Ethiopian News and Views.

በኢትዮጵያ የፍትህ ጋዜጣ አዘጋጆች (የፍትህ ቤተሰቦች) እንደገና ወደ አደባባይ ተመለሱ

ተመልሰናል!

አባይ ሚድያ – አዲስ ታይምስ

                        ከሁለት ወራት በፊት የፌደራሉ ዐቃቤ ሕግ “ለሀገር ደህንነት የሚያሰጋ ዘገባ” በሚል ምክንያት የ2004 ዓ.ም ሐምሌ አስራ ሶስቱን የፍትሕ ጋዜጣ እትም አገደ፡፡  በቀጣዮቹ ሳምንታት ደግሞ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ቀጥተኛ ባልሆነ ትእዛዝ በተላለፈለት ውሳኔ ፍትህ ጋዜጣን ማተም እንደማይችል ነገረን፡፡  እናም ፍትህ ጋዜጣ በስርአቱ መሪዎች ፖለቲካዊ ውሳኔ ወደ ገበያ እንዳትመለስ

ከታገደች ሁለት ወራቶች አለፉ፡፡  በዚህ ሁኔታ ውስጥ ላለፉት ሁለት ወራት እንድንቆይ ብንገደድም ምርጫችን ሁለት ነበር፡፡  በአቶ መለስ ከመሪነት መራቅ ወዲህ ወደ መንበሩ የመጡት ገዢዎች እንደተመኙት ከአደባባይ ርቀን መቆየት አልያም ሌላ አማራጭን ተጠቅሞ ወደ አንባቢዎቻችን መድረስ፡፡  እነሆ እኛም በተደጋጋሚ እንዳልነው “ዝም ማለት አይቻለንምና” በዚህ መልኩ ወደ አደባባይ ተመልሰናል፡፡

ከመጽሔት ስያሜ እና ከቅርጽ ውጪ አንባቢዎች በዚህች መጽሔት እና በተወዳጇ ፍትህ ጋዜጣ መካከል አንዳችም ልዩነት እንደሌለ እ

ንደሚገነዘቡ እናምናለን፡፡  በፍትህ ጋዜጣ የምትከታተሏቸው ፀሐፊዎችም ሆኑ የፀሐፊዎቹ ሙግቶች ከዚህ እትም በኋላ በአዲስ ታይምስ መጽሔት በኩል ታገኛችኋላችሁ፡፡  እናም በዚህች መጽሔት ላይ እንደሁልጊዜውም ለሀገራችን እና ለህዝባችን ይጠቅማሉ ብለን በምናምናቸው ጉዳዮች ላይ ከለአንዳች ፍርሀት እና ማንገራገር መፃፋችንን እንቀጥላለን፡፡  ካለአንዳች ፍርሀት እና ማንገራገር መረጃዎችን እናስተላልፋለን፡፡

“ፍትህ ጋዜጣ” መስዋዕት የሆነችውም ያለፍራች በዘገበችው ዜና መሆኑም ይታወቃል፡፡  ምንአልባትም ዜናን አማርጦ የመስራት ወይም የሚደፈር እና የማይደፈር ጉዳይን ለይተን መስራት ብንመርጥ ኖሮ “ፍትህን“ የሚያህል ዋጋ አንከፍልም ነበር፡፡  ፍትህንም በዚህ መልኩ አናጣትም ነበር፡፡  ሆኖም ደጋግመን እንጽፍ እንደነበረው ምንጊዜም የምንቆመው ከእውነት እና ከሕዝብ ጋር ነውና በዛን አስቸጋሪ ወቅት ሚዲያው በተፈተነበት ወቅት ያለአንዳች መወላወል ቃላችንን አክብረን አቋማችንን አሳይተናል፡፡  እናም ምንም እንኳ የተነጠቅነው ህልማችንን ቢሆንም ምንም እንኳ የከፈልነው ዋጋ የመረረ ቢሆንም ለቃላችን እና ለእውነት መገዛታችን ዛሬ አንገታችንን እንዳንሰብር አድርጎናል፡፡

በወቅቱ ለፍትህ መታገድ ምክንያት የነበረው ዜና ከአንድ ወር በኋላ በራሱ ፍትህን በአፈነው ሃይል ይፋ መሆኑ ይታወቃል፡፡  ይህንንም ተከትሎ በእነዛ ወሳኝ ቀናት፤ በእነዛ የፈተና ቀናት፤ በእነዛ የቁርጥ ቀን ሕዝብን የሚያሳስት መረጃ ሲያስተላልፉ የነበሩ ጋዜጦች ዛሬ አንገታቸውን ሰብረው ይቅርታ እየጠየቁ ነው፤ ይቅርታ ያልጠየቁት ደግሞ ይቅርታ ይጠይቁ ዘንድ ግዴታቸው ነውና እንጠብቃለን፡፡  ይቅርታ የጠየቁትንም ከዚህ በኋላ ይህን ስህተት አይደግሙም በሚል ቀናነት የይቅርታ ቃላቸው ዋጋ ያገኝ ዘንድ ምኞታችን ነው፡፡

ሌላው የአዲስ ታይምስ ርእሰ አንቀጽ ትኩረት በአቶ ኃይለማርያም መሪነት ሀገሪቱን ለመምራት ለተዘጋጀው ገዢ ቡድንም ሁለት መልእክቶች ማስተላለፉ ላይ ነው፡፡  የመጀመሪያው እና ቀዳሚው ካላንዳች ፍትሀዊ (ዐቃቤ ሕግ ጋዜጣችን እንድትታገድ ጠይቆ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጓል) እና ርትአዊ እርምጃ በብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት በኩል ጋዜጣችንን እንዳናሳትም የተቀመጠብን ኢ-ሕገ መንግስታዊ ዕግድ እንዲነሳ እንጠይቃለን፡፡  በስልሳ ሺህ ወጣቶች ደም ቆሟል የሚባለው ሕገ-መንግስት ለዜጎች ከሰጠው መብቶች መሀከል አንደኛው የመናገር እና የመጻፍ ነጻነት እንደሆነ ይታወቃል፡፡  ስለሆነም ከሟቹ መለስ በባሰ መልኩ አዲሶቹ መሪዎች ሕገ-መንግስቱን እየናዱ መቀጠል የለባቸውም፡፡  አዲሱ አመራር የመለስን  “ራዕይ” መከተል ብቸኛው ምርጫ አድርጎ ሲወስድ፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በምሬት ከሚተቹባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መሀከል አንደኛው የፕሬስ ነጻነትን አለማክበር በመሆኑ ተከታዮቻቸው ይህን የመሪያቸው ክፉ ውርስ እንዳይቀጥል መስራት እንዳለባቸው አጥብቀን እናስገነዝባለን፡፡

ሁለተኛው መልእክታችን ኢህአዴግ ቅጥ ባጣ አንባገነናዊ መንገድ ሀገሪቱን ለሁለት አስርታት ገዝቷል፡፡  በአገዛዙ ውስጥ የተደረጉ ሀገራዊ ምርጫዎች ካለፍትሃዊነት የስርዓቱን አሸናፊነት ብቻ እንዲያስረግጡ ተደርገዋል፡፡  የገዢውን ቡድን ፖለቲካዊ የበላይነት ለመገዳደር የሞከሩ ድምጾች በግድያ፤ በእስር እና በስደት ከአደባባዩ ተገልለዋል፡፡  በዚህ መንገድ ለመግዛት መሞከር ምን አይነት ሀገራዊ ክስረት ውስጥ እንደጣለን ሁላችንም እናውቃለን፡፡  ስለሆነም አዲሱ አመራር ኢህአዴግ እስዛሬ ከመጣበት መንገድ በተሻለ ፖለቲካዊ ምህዳሩን እንዲያሰፋ፤ አፋኝ ህግጋቶቹን እነዲያነሳ እና በሕገ-መንግስቱ የተፈቀዱ የዜጎችን ሁለንተናዊ መብቶች ካለምንም መሸራረፍ አክብሮ እንዲያስከብር እንጠይቃለን፡፡  ከዚሁ ጋር በተዛመደ እየተንቆለጳጰሱ የሚቀርቡልን የባለ “ራዕዩ” የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውርሶች እንደገና እንዲፈተሹ እንጠይቃለን፡፡  ተገኝቷል የሚባለው የኢኮኖሚ እድገት ዜጎችን ካለውዴታቸው በማፈናቀል የሀገር መጪ ጊዜያትን በሚያጨልም መንገድ ለሌሎች መንግስታት እና ተቋማት ለም መሬቶችን በመስጠት የብዙሃኑን ዜጋ የኑሮ ውድነት መግራት ያልቻለ እድገት አልፎም በግዳጅ እና ርትዐዊ ባልሆነ አካሄድ በሚሰበሰብ ግብር ላይ የተመሰረተ ነውና ይህ የፖሊሲ አካሄድ እንደገና በቅጡ እንዲፈተሽ ማስታወስ ዜግነታዊ ግዴታችን ነው ብለን እናምናለን፡፡  ይህ ስርዓት በቀድሞው መሪው ባህል እቀጥላለሁ የሚል ከሆነ ራሱንም ሆነ ሀገሪቱን ወደ አዘቅት ሊከታት እንደሚችል ማስታወስ ያሻል፡፡

Comments (1)

Leave a Comment

© 2007-2012 Abbay Media ‘The Ethiopian Information Bank’

Scroll to top