Ethiopian News and Views.

የመጅሊስ ምርጫው ያለስምምነት እንደቀጠለ ነው

አባይ ሚድያ / ሰንደቅ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ወይም መጅሊስ ምርጫ በቀጣዮቹ ተከታታይ ሳምንታት የሚካሄድ ሲሆን ባሰለፍነው ሳምንት ምርጫውን የሚያካሂዱ እና የሚታዘቡ አካላት እጅ በማውጣት በየቀበሌው እና ትምህርት ቤት አዳራሾች በተካሄዱ የምርጫ ስነ-ስርዓቶች ተካሂደዋል፡፡  በቀጣይ እስከ ጥቅምት 20 ቀን 2005 ዓ.ም የቀበሌ፤ የወረዳ፤ የዞን፤ የክፍለ ከተማ፤ የክልል እና የፌደራል የመጅሊስ አመራሮች ይመረጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኡላማዎች ምክር ቤት ምርጫውን በገለልተኝነት እያከናወነ እና በተሳካ ሁኔታ እያስፈጸምኩ ነኝ ቢልም ምርጫው የሁሉንም ሙስሊሞች ይሁንታ አላገኘም በሚል ቅሬታ እንደቀጠለ ነው፡፡  ቅሬታው ምርጫውን እያከናወነ ባለው የኡላማዎች ምክር ቤት ላይ ጭምር ነው፡፡  ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ምርጫ የማስፈጸም እድል እንደሌለው እና የተቋቋመውም በቀድሞው መጅሊስ አባላት (በፈረስው የቀድሞው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት) መሆኑን በመጥቀስ በዚሁ ምርጫ የቀድሞው መጅሊስ እራሱ ያዘጋጃቸውን ሰዎች ቦታው ላይ ለማስቀመጥ ነው የሚል ቅሬታ እየቀረበ ነው፡፡  በዚህም ምርጫ ስልጣን ይይዛሉ ተብለው የሚገመቱ ስልጠና የወሰዱ እና ከኢትዮጵያ ውጭ በሊባኖስ ስልጠና ያገኙ እና በቀድሞ መጅሊስ የሚደገፉ እንደሆኑ እንደሚገመት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ፡፡  በመሆኑም አዲሱ ይመረጣል የተባለው አመራር የቀድሞውን መጅሊስ ስራ የሚወርሱ እንጂ እራሱን ችሎ አስቦ የሚሰራ አይደለም እያሉ ነው፡

በሌላ በኩል ምርጫው በቀበሌ መዋቅር ውስጥ መካሄዱ መንግስት ጣልቃ መግባቱን ሙሉ በሙሉ ያሳያል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች ቀደም ሲል የቀበሌ አዳራሾች ለትብብር ይጠየቁ እንደሆን እንጂ እንዳሁኑ ምርጫው በመንግስት መዋቅር ውስጥ አልገባም ነበር ሲሉ ይቃወማሉ፡፡  በተጨማሪም ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከመንግስት ጋር ያደራድሩኛል ብሎ የመረጣቸው ሰዎች እስር ላይ ሆነው ምርጫው መካሄዱ አግባብ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ሕዝብ የወከላቸው ሰዎች እስር ቤት ተቀምጠው ምርጫ ማካሄድ ተገቢ አለመሆኑን የሚጠቅሱት የምርጫው ተቃዋሚዎች በእስር ላይ ያሉት ሰዎች በአወሊያ በቀጥታ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ተመርጠዋል ሲሉም ያረጋግጣሉ፡፡  የታሰሩት ሰዎች በሙስሊሙ ስለመመረጣቸው ተጨባጭ ማስረጃ መኖሩን እና የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሚያውቀው ጉዳይ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡  ከተመረጡት ውስጥ የኢህአዴግ አባል የሆኑ ሙስሊሞችም እንዳሉበትም ይየገልጻሉ፡፡  በመሆኑም ምርጫው ከመካሄዱ በፊት የታሰሩት 17 ሰዎች መፈታት አለባቸው ይላሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የምርጫው አካሄድ ላይ በርካታ ችግሮች መኖራቸውንም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ፡፡  ምርጫው በህግ እየተመራ አይደለም ሲሉ ይከሳሉ፡፡  ሙስሊሞች በግዴታ ለምርጫው እንዲመዘገቡ መደረጉንም አማረዋል፡፡  በምርጫው ያልተሳተፉ የእምነቱ ተከታዮች ላይ ልዩ ልዩ ችግሮች እያጋጠሙ መሆኑን አብራርተዋል፡፡  በተለይ በክልሎች ያለው ምርጫ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት በመጥቀስ በአጠቃላይ ምርጫው ተአማኒነት የለውም ብለዋል፡፡  ከዚህ በተጨማሪ በአሁኑ ምርጫ የቀድሞው መጅሊስ አባላት በአሁኑም ምርጫ እንዲሳተፉ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

የቀድሞው የመጅሊስ አባላት በምርጫው ይሳተፋሉ ስለሚለው ቅሬታ አቶ መሐመድ ረሺድ በኢትዮጵያ ኡላማዎች ምክር ቤት ዋነኛ የምርጫ አስተባባሪ እና አማካሪ  ተጠይቀው ሲመልሱ ዋናው ነገር የቀድሞው መጅሊስ እንደተቋም ችግር ቢኖርበትም በቀድሞው መጅሊስ ውስጥ ጠንካራ ግለሰቦች መኖራቸውን መዘንጋት የለበትም ሲሉ መልሰዋል፡፡

Leave a Comment

© 2007-2012 Abbay Media ‘The Ethiopian Information Bank’

Scroll to top