Ethiopian News and Views.

ወ/ሮ አዜብ መስፍን እስካሁን ቤተመንግስቱን ለአቶ ኃለማርያም አላስረከቡም

መስከረም ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢሳት ዘጋቢ እንደገለጠው ወ/ሮ አዜብ መስፍን ቤተ መንግስቱን ለቀው ባለመውጣታቸው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም  ደሳለኝ  ቦሌ ከሚገኘው ቤታቸው ጠዋት እና ማታ ሲገቡና ሲወጡ መንገድ እየተዘጋ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ እየተፈጠረ ከመሆኑም በላይ ከአሁኑ የአካባቢውን ነዋሪዎች እያስመረሩ ነው፡፡

በርግጥ ሥራቸውን ጠ/ሚኒስትር ቢሮ እየገቡ በመስራት ላይ መሆናቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ወ/ሮ አዜብ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል እንደሚገኙ ቢገለጽም ጉዳዩን ከነጻ ወገን ለማጣራት ያደረግነውጥረት አልተሳካም፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለፕሬዚዳንትነት ተመርጠው ቃለመሃላ ከፈጸሙ በኃላ ወዲያውኑ የተወሰዱት ወደ ቤተመንግስት እንደነበር በእርሳቸው የህይወት ታሪክ  ላይ የተጻፈው  ”ዳንዲ የነጋሶ መንገድ ” የሚለው መጽሀፍ ያመለክታል። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ግን እስካሁን ድረስ ምንነቱ ባልታወቀ ምክንያት ወደ ቤተመንግስቱ አልገቡም:: በቤተመንግስቱ ቅጥር ግቢ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ ባለው ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ውስጥ ለመግባት አቶ መለስና ቤተሰባቸው ባይታደሉም ህንጻው እየተጠናቀቀ በመሆኑ አቶ ኃለማርያምና ቤተሰቦቻቸው በቅርቡ ይረከቡታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአቶ ሀይለማርያምን ሹመት ያልተቀበሉት በርካታ የኦህዴድ ከፍተኛ  የአመራር አባላት የማእከላዊ ስብሰባቸውን በአዳማ ከተማ እያካሄዱ ነው።

የስብሰባውን ሂደት በተመለከተ መረጃዎች እንደደረሱን እናቀርባለን።

Leave a Comment

© 2007-2012 Abbay Media ‘The Ethiopian Information Bank’

Scroll to top